የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ በካሄዳው 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን

የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5 ፓርላማ ዘመን 5 ዓመት የሥራ ጊዜ በካሄዳው 2 መደበኛ ስብሰባውን የ2012 ምርጫ አራዘመ፤ የህዝብና ቤት ቆጠራን አራዘመ፤ አዲስ አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤም መረጠ

 

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኙ ስጋት እስካለ ድረስ የሁሉም ምክር ቤቶች ስልጣን እንዲቀጥል፣ እንዲሁም የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወረርሽኙን የጤና ስጋት አይደለም ብለው ካወጁ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንኑ ካጸደቀ በኋላ 9 ወር እስከ አንድ ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ምርጫ ይካሄድ የሚለው የውሳኔ ሃሳብ 114 የድጋፍ ድምፅ፣ 4 ተቃውሞ፣ 1 ድምፀ ተዓቅቦ  አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በስብሰባው ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የተራዘመው የህዝብና ቤት ቆጠራ አሁንም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለህዝብ ጤናና ደህንነት ሲባል እንዲራዘም ወስኗል።የሚመለከታቸው አካላት የቫይረሱን ስርጭትና ጉዳት ገምግመው መቀነሱን ወይንም ጉዳት ማድረሱ ማቆሙን ማረጋገጥ ሲችሉ ቆጠራው በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲካሄድ ወስኗል።ምክር ቤቱ የተመለከተው ሌላው ጉዳይ በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉትን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ነው።

 

በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የዞን ምክር ቤቶች የቀረቡ የክልልነት ጥያቄዎችን ምላሽ ለማሰጠት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው የመነሻ ምክረ ሃሳብ በሌሎች ሃሳቦች ዳብሮ የመጨረሻ ውሳኔ በራሱ በኮሚቴው እንዲሰጥበት ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል።

 

የከፋ፣ የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የከምባታ ጠምባሮ፣ የሃዲያ፣ የጋሞ፣ የጉራጌ፣ የጌዴኦ፣ የጎፋና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ማቅረባቸውን ኮሚቴው ገልጿል።

 

በመሆኑም የክልልነት ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ የጋራ መድረኮችን የማመቻቸት፣ የምክር ቤቱን አስፈጻሚ ከክልሎች አስፈጻሚዎች ጋር የማገናኘትና የማወያየት፣ ከዚህ ቀደም የተጠኑ ጥናቶችንና የሰላም አምባሳደሮችን ስራ እንዲሁም ህዝብን በማወያየት የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ ቋሚ ኮሚቴው ይዞ እንዲቀርብ በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ ተወስኗል።

 

ምክር ቤቱ በመጨረሻ በቅርቡ በፈቃዳቸው ስልጣን በለቀቁት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ምትክ አቶ አደም ፋራን ከሱማሌ ክልል አፈጉባኤ አድርጎ መርጧል።

 

ቀደም ሲል የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ የነበሩት አቶ መሐመድ ረሽድ ዛሬ በአፈጉባኤነት ከተመረጡት ጋር ከአንድ ክልል የተወከልን በመሆኑ ለሌሎች እድል መስጠት ይግባል በሚል በፈቃዳቸው ሀላፊነታቸውን ለቀዋል።ም/ቤቱ በምትካቸው ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በምክትል አፈጉባኤነት ተመርጠዋል።