ሁሉንም ዜጋ ያስደነገጠ ተግባር የተፈፀመበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ታስቦ ዋለ።
ጥቅምት 24 ቀን ከሃዲውና ሀገር አፍራሹ አሽባሪው የህወሃት ጁንታ ቡድን በአገራችን በሰሜኑ ዕዝ በጀግናው መከላኪያ ሰራዊታችን ክህደት የፈፀመበትና ዘግናኝ ጭፍጨፋ ያካሄደበት ቀን በመሆኑ "አልረሳውም፣ እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጽ/ቤቱ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በተገኙበት በህሊና ፀሎት፣ በሻማ ማብራት ስነስርዓት እና በውይይት ተዘክሮ ውሏል፡፡
ዝክረ ቀኑን በንግግር የከፈቱት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ም/አፈ ጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ዛህራ ሁመድ ሲሆኑ ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን የሁሉም ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቁርጥ ቀን ልጆች ወንዱንም፣ ሴቱንም እንዲሁም ሁሉንም ሃይማኖቶችና እምነቶች የሚወክሉ የሀገር አለኝታ ናቸው በማለት ያላቸውን አድናቆትና አክብሮት ገልጸዋል፡፡ በማከልም መከላከያ ሰራዊታችን የትግራይን ሕዝብ ከጠላት ጥቃት ሲጠብቁ ለሁለት አስርተ ዓመታት ያህል አብሮ ከመኖሩም በላይ በልማታዊ መስኮች በመሰለፍም የሕዝብ አለኝታ እንደነበሩና ዳሩ ግን ከኢትዮጵያዊያን ባህልና ወግ ባፈነገጠ መልኩ አንበጣ ሲከላከሉና እህል ሲያጨዱ የዋሉትን የሰራዊት አባላት እራት በመጋበዝ አፍነው ዘግናኝ ጭፍጨፋ አካሄደውባቸዋል፡፡
ስለሆነም የተከዳው እና የተጨፈጨፈው መከላከያ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ሲሉ ቀኑን ጥቁር ቀን በማለት አሰታውሰዋል፡፡ ቀኑን ስንዘክር በተሰማራንበት የስራ መስክ ሁሉ የተሠዉ ጀግኖቻችን እያስታወስን አኩሪ ገድል በመፈፀም የሚጠበቅብን የዜግነት ግደታችንን እንድንወጣ በአጽንዖት መልዕክታቸው አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠልም የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ሕዝብ እና ሕገ መንግስት በሚል ርዕሰ ጉዳይ አቶ ትግሉ መለሰ የበይነ-መንግስታት ግንኙነት፣ ብዝሃነትና የዲሞክራሲ ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አጭር ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጓበታል፡፡