በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፋ ተቋማዊ የአሰራር ሪፎርም የምክር ቤቱ ሕገመንግሥታዊ ተልዕኮውን ውጤታማ እንደሚያደርገው ተገለፀ ፤

ነሐሴ 29 / 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ፦ /በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት/ በምክር ቤቱ ሪፎርም ስራ ላይ ለተሳተፉት ተቋማትና ተባባሪ አካላት በተዘጋጀው የምስጋና፣ የዕውቅናና የሽልማት ስነስርዓት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ አደም ፋራህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ አንቅጽ 62 እና አግባብ ባላቸው ሕጎች የተሰጡትን ተግባራትን እንዲሁም የምክር ቤቱን ጽ/ቤት ለማቋቋም በወጣው አዋጅ በተመለከቱት ስልጣንና ተግባራት መሰረት በሕዝቦች መካከል ፍትሕ ፣እኩልነትና ዲሞክራሲያዊ አንድነት ስር እንዲሰድና ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመገንባት ሂደት ላይ ሪፎሪሙ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፋ ተቋማዊ የአሰራር ሪፎርም የምክር ቤቱ ሕገመንግሥታዊ ተልዕኮውን ውጤታማ እንደሚያደርገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ አደም ፋራህ በመግለፅ ሪፎርሙ የምክር ቤቱን የአስር ዓመቱን መሪ ዕቅድ ለማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ተብለዋል ። የብሔር ማንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ሚዛነዊነትን ከማስጠበቅ ረገድ፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ከመመለስ፣ በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት ከማረጋገጥ አንጻር ፣ የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓልን ለአገር አንድነት፣ ለእኩልነት እና ለብልጽግና ጉዞዎችን ከዳር ለማድረስ ሪፎርሙ ወሳኝ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል ፡፡ አክለውም ምክር ቤቱ የተጣለበትን ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት እኩልነት፣ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲሰፍን ለማደረግ በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፋ ተቋማዊ የአሰራር ሪፎርም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከተባባሪ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ መንግስታዊ ራዕይና ተልዕኮን በብቃትና በጥራት ለመፈጻም የተሻለ ይሆናል ሲሉ ገልጻዋል፡፡ ከዚህ በፊት በምክር ቤቱ በዋና ዋና አራት የትኩረት ዘርፎች ጥናትና ምርምር የሚደረግባቸው ዓላማ ፈጻሚ ዘርፎች ተለይተው መቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ከዘህ አንጻር ሀገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ ውጤታማ የፊሲካል ሽግግር እና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የሕገ መንግስት የበላይነትን ማረጋገጥ እና ተቋማዊ የማስፈጻም አቅም ግንባታ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በመጨረሻም አፈ ጉባዔው በምክር ቤቱ ሪፎርም ስራ ላይ የተሳተፉትን ተቋማትና ተባባሪ አካላትን በማመሰገን ምክር ቤቱ ወደ ፊት ከነዚህ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ተባባሪ አካላትም በበኩላቸው ከምክር ቤቱ እያደረገ ያለውን ሪፎርም ከማድነቅም ባሽገር ምስክር ነን ሲሉ ገልጸዋል ። ከምክር ቤቱ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነትና ፍላጎት አሳይተዋል፡፡